አዲስ የተቋቋመው የጠበቆች ማኅበር ለዜጎች ምን አበርክቶ ይኖረዋል?

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር ሲባል ሰምተው ይሆናል። ማኅበሩ አሁንም አለ።

እንደ አንድ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበር በተለይም የአባላቶቹን መብት ለማስጠበቅ የተለያዩ ሚናዎችን ቢወጣም ባሳለፍነው ሳምንት ከተቋቋመው የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማኅበር ግን በእጅጉ የተለየ ነው።

በመላው ዓለም በተለይም የ’ባር አሶሴሽን’ በመባል የሚታወቁት እነዚህ የሕግ ሙያ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርባቸው ተቋማት ሲሆኑ፤ መንግሥታት፣ ግዙፍ ኩባንያዎች እንዲሁም ሙያውን የሚተገብሩ የሕግ ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ የቁጥጥር ሚና እና ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፍትህ አሰጣጥ ታሪክ ለበርካታ ጊዜ ታልሞ ነገር ግን ሳይተገበር የቆየው ይህ ማኅበር ሐምሌ 29/2013 ዓ.ም በጸደቀው የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ መሰረት እውን ሆኗል።

“ጠበቆች በመላው ዓለም አብዛኛውን ሕብረተሰብ በመወከል የሚከራከሩ፣ የሕግ ምክር የሚሰጡ እና በየቀኑ እስከታች ካለው ዜጋ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። የእነሱ መጠየቅ ለዐቃቤ ሕግም ሆነ ለዳኞች ተጠያቂነት ያለው የፍትህ ሥርዓት ከፍተኛ ሚና አለው” ሲሉ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው ይናገራሉ።

“የፍትህ ሚኒስቴር ከሦስት ዓመት በፊት በጀመረው ሥራ ለረጅም ዓመታት ሲጓተት ቆይቶ የማቋቋሚያ አዋጁን ለማዘጋጀት ተችሏል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመንግሥት ደረጃ የዚህ የጠበቆች ማኅበር መቋቋም አስፈላጊነት ከታመነበት ለምን እስካሁን ሳይቋቋም ቀረ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “በተለያዩ ጊዜኣት የተለያዩ የሕግ ረቂቆች ተዘጋጅተው ነበር። ነገር ግን የመንግሥት ቁርጠኝነት ስላንነበረ ነው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

በርካታ የመገናኛ ብዙኅን ሲዘግቡት የቆየው የዚህ ማኅበር መቋቋም ጉዳይ በርግጥም ለእያንዳንዱ ዜጋ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ የሚለውን እንቃኝ።

አዋጁ ምን ይላል?

ኢትዮጵያ ውስጥ እስካለፈው ሐምሌ ድረስ ጠበቆች በጋራ ተሰባስበው ሕጋዊ ሰውነት ያለውን የሕግ ኩባንያ ማቋቋም አይችሉም ነበር።

በዚህም አንድ ጠበቃ በተሰጠው የጥብቅና ፈቃድ መሰረት የጥብቅና ቢሮ ከፍቶ ይስራ እንጂ የጥብቅና ድርጀቶችን (ሎው ፈርም) በሽርክና ከፍቶ መስራት አይችልም ነበር።

የጥብቅና ድርጅቶች በሥራቸው በተለያየ የሕግ ዘርፍ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን የያዘ እና ከመደበኛ የጥብቅና ሥራ በዘለለ በርካታ ተግባራትን የሚያከናውኑ ናቸው።

ታዲያ ይህ አዲሱ የጠበቆች ማኅበር ከግለሰብ ጠበቆች ውጪ እነዚህን ሕጋዊ ሰውነት ያላቸውን የጥብቅና ድርጅቶች ያቀፈ በመሆኑ የበለጠ ግዙፍ ያደርገዋል።

ማኅበሩ አስገዳጅ (ስታቹተሪ) መሆኑን አዋጁ ያስቀምጣል። ይህም ማለት ማንኛውም ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት የጥብቅና ፍቃድ ሲሰጠው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የማኅበሩ አባል ይሆናል።

የማኅበሩ ገቢ እና የአባላቱ መዋጮ እስከሚጠናከር እና ራሱን እስከሚችል ድረስ መንግሥት እንደሚደግፈው ተደንግጓል።

ማኅበሩ ካሉት ክፍሎች ውስጥ ከፍተኛው ሥልጣን ያለው ሰባት አባላት የሚኖሩት ሥራ አስፈጻሚው ሲሆን ይህም በጠቅላላ ጉባኤው የሚመረጥ ይሆናል።

ጥር 15 በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤም ሂሩት መለሠ 634 ድምጽ፣ ፊሊጶስ አይናለም 628 ድምጽ፣ ሊቁ ወርቁ 522 ድምፅ፣ ዮሴፍ አዕምሮ 514 ድምጽ፣ ሆሳዕና ነጋሽ 492 ድምጽ፣ ትደነቂያለሽ ተስፋ 424 ድምጽ፣ ሰለሞን እምሩ 418 ድምጽ በማግኘት ማኅበሩን እንዲመሩ ተመርጠዋል።

እንዲሁም ማኅበሩ ስንዱ አለሙን ፕሬዝዳንት፣ ቴዎድሮስ ጌታቸውን ምክትል ፕሬዝዳንት በማድረግ መርጧል።

የጠበቆች ማኅበሩን የሚከታተል ቦርድ በዚሁ አዋጅ የተቋቋመ ሲሆን በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቅራቢነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ ሰባት አባላት ይኖሩታል።

ከአባላቱ ሦስቱ ከጠበቆች ማኅበሩ፣ አንድ የሕግ መምህር፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድ እንዲሁም ሁለት አባላት ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይሾሙለታል።

በሕግ እና በፖሊሲ አወጣጥ ላይ

ጥር 15/2013 ዓ.ም የተካሄደው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ ከ 1 ሺህ 600 በላይ የሕግ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን ከአምስት ሺህ በላይ የፌደራል ጠበቆች አባላት ናቸው።

ይህ ማኅበር ይዞት ይመጣል ተብሎ ከሚጠበቁ ነገሮች አንዱ በሕግ እና በፖሊስ አወጣጥ ላይ የሚጫወተው ሚና ነው።

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ለቢቢሲ እንደገለጹት ማኅበሩ መንግሥትን የመቆጣጠሪያ፣ ሙያውን የማሳደጊያ ብሎም በሂደቱ ለሕዝብ የሚቆም ተቋም እንዲሆን ታልሞ መቋቋሙን ይናገራል።

እስካሁን የነበሩት የሕግ ማኅበራት እንደማንኛውም የሲቪክ ማኅበራት ከምዝገባ የሚመነጭ እንጂ ከሕግ የሚመነጭ ሥልጣን ስላልነበራቸው አዳዲስ ሕጎች ሲወጡ ሊያሳድሩ የቻሉት ሚና የተገደቡ መሆኑን ቴዎድሮስ ይናገራሉ።

“አዲስ የሚወጡ እና የሚሻሻሉ ሕጎች የዜጎችን ሰብአዊ መብቶችን ያረጋገጡ እና ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ጫና ያደርጋል። ጥሩ ሕጎች ከወጡ በኋላም የፖለቲካ ሥልጣን በያዘው አካል ሕጎች እንዳይሸረሸሩ የራሱን ሚና ይወጣል። እንዲሁም ፍርድ ቤቶች በሕግ ትርጉም ወቅት ያልተገባ ጫና እንዳይፈጠርባቸው ተከታትሎ የማጋለጥ እና የመታገል ጥሩ እድል የሚፈጥር ነው” ሲሉ ቴዎድሮስ ይናገራሉ።

በሕግ ትምህርት ጥራት ላይ

በዓለም ካሉ ተመሳሳይ ማኅበራት አንዱ የሆነው የአሜሪካ የባር አሶሲየሽን ከተቋቋመበት 1878 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በሕግ ትምህርት ጥራት ዙሪያ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

እ.ኤ.አ. በ1921 ለሕግ ትምህርት ጥራት ዝቅተኛ መመዘኛዎችን ብሎም እነዚህን መመዘኛዎች የሚያሟሉ የሕግ ትምህርት ቤቶችን ይፋ አድርገው እንደነበር በዘርፉ የተሰነዱ ጽሁፎች ያሳያሉ።

እ.ኤ.አ. በ1952 የአሜሪካ መንግሥት የጠበቆች ማኅበሩ የሕግ ትምህርት ቤቶችን ጥራት በመቆጣጠር የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጥ ፈቅዶ፣ በአሁኑ ወቅት ከጥቂት ዓለም አቀፍ ተቋማት ውጪ ሁሉም የሕግ ትምህርት ቤቶች ብቃታቸው በዚህ ማኅበር ተለከቶ ነው ማረጋገጫ የሚያገኙት።

በኢትዮጵያም የተቋቋመው አዲሱ የጠበቆች ማኅበር ተግባር እና ኃላፊነቱን በሚዘረዝረው የአዋጁ ክፍል ላይ ማኅበሩ የሕግ ትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተጠቅሷል። በተደጋጋሚ የሚነሳው የሕግ ትምርት ቤቶችን ጥራት ማስጠበቅ አንደኛው የማኅበሩ ሚና እንደሚሆን ቴዎድሮስ ተናግረዋል።

ያው ገለልተነት እና ጥንካሬ ላይ

የሙያውን ከፖለቲካ ጫና ነጻ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይህ ማኅበር በተለይም በዲሲፕሊን ክስ ጠበቆች ላይ የሚደርስን ጫና በማስቆም ቀጥተኛ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የጠበቆችን ሥነ ምግባር የሚከታተለው እና አስከ ፍቃድ መንጠቅ ድረስ የሚደርሰው ሥልጣን የዲሲፕሊን ኮሚቴው የሚተዳደርበት መንገድ አንዱ የተለወጠው ነገር እንደሆነ ቴዎድሮስ ይናገራሉ።

“ከዚህ ቀደም የዲሲፕሊን ኮሚቴው ውሳኔዎች በፍትህ ሚኒስቴር ሊለወጡ እና ሊሻሩ ይችሉ ነበር” የሚሉት የማኅበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት “አሁን ግን የዲሲፕሊን ኮሚቴው ውሳኔን ማሳወቅ እንጂ ከዚያ ያለፈ ሥልጣን ለፍትህ ሚኒስቴር አይሰጥም። ነገር ግን ገና የሚቋቀመው ቦርድ በይግባኝ ያየዋል” ሲሉ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።

ቴዎድሮስ እንደሚሉት ይህ ማኅበር የሕግ ባለሞያዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል መሆኑን እና ለተወሰነ ጊዜ ግን የመንግሥት ከፊል ቁጥጥር እንደሚቀጥል ይናገራሉ። ነገር ግን በጉባኤው ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ ይዞ የሚቀጥለው ራሱ ማኅበሩ መሆኑን ያስረዳሉ።

በሩ በሕግ የተሰጠውን መብቶች ይፈጽመው ይሆን?

የአዋጁ አንቀጽ 98 ቦርዱ እና ማኅበሩ በሕግ የተሰጣቸውን ተግባር እና ኃላፊነቶች በሁለት ዓመት ውስጥ ይረከባሉ ሲል ይደነገግጋል።

ይህም በ 2016 ዓ.ም ክረምት ላይ ይህ የጠበቆች ማኅበር ሥራውን ማከናወን ይጀምራል ማለት ነው።

“ተቋሙ በቂ የሰው ኃይል፣ ቁሳቁስ እና የማደራጀት ሥራዎችን እየሰራ የሚቆይ ሲሆን፤ ነገር ግን ቀደም ብሎ ወደ ሥራ መግባት ይቻላል” ይላሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቴዎድሮስ።

ከዚህ ቀደም የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር አዲስ በሚረቀቁ ሕጎች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን ቴዎድሮስ ይናገራሉ። በምሳሌነትም የሲቪክ ተቋም የሆነው የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ለመጽደቅ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ የነበረውን አዲሱን ወንጀል ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተመልሶ ማሻሻያዎች እንዲደረጉበት ያስቻሉ ጫናዎች ማድረጉን ያስታውሳሉ።

የበለጠ ሥልጣን በተሰጠው በጠበቆች ማኅበር በኩል መንግሥት በትክክለኛው ሕግ መሰረት ሥራውን እንዲያከናውን ጫና እንደሚያደርጉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሕግ የበላይነት እና በአገሪቱ የሚሰጠው የፍትህ አገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል፣ በተለይም ጠበቆች የሚሰጡት አገልግት ጥራት እንዲጠበቅ እና በሥነ ምግባር የሚሰጥ እንዲሆን ማኅበሩ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ የሆኑ በተለይም የዴሞክራሲ እና የሙያ ማኅበራት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ጊዜ መልሰው በአስፈጻሚው ሲጠለፉ እና የተቋቋሙለትን አላማ ከማሳካት ይልቅ የመንግሥትን ሃሳብ ያስፈጽማሉ የሚል ወቀሳ ይነሳባቸዋል።

ከዚህ አንጻርም ብዙ የተባለለት የጠበቆች ማኅበር ከዚህ ጫና ወጥቶ በሕግ የተሰጠውን ተግባር ለመፈጸም ምን ማስተማመኛ አለው? ለሚለው ጥያቄ “የአንድ ማኅበር ስኬት የሚወሰነው በሁለት ነገር ነው። አንደኛው በአባላቱ ጥንካሬ ሲሆን ሌላው የፖለቲካ ሥልጣን በያዘው አካል ቁርጠኝነት ነው። በጋራ ተደጋግፈው ካልሆነ ለውጥ ማምጣት ይከብዳል” ሲሉም ቴዎድሮስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

About the Author

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may also like these

No Related Post